A SHORT HISTORY OF OUR CHURCH
The Holy Trinity Ethiopian Orthodox Tewahedo Church (“Holy Trinity”) has the honor of being the first Ethiopian Orthodox Church not only in the Charlotte area, but across both Carolinas.
![]() |
Holy Trinity was formed in August 1999 in Charlotte through the tireless efforts of our founders, Ato Tedla Fantaye, Ato Estifanos Assefa and Ato Yosef Abraha. These three servants of the Holy Trinity mobilized additional visionaries: Wzo. Fantaye Gemeda, Wzo. Abebech Assefa, Dr. Tekle Ayano, Ato Belay Gebreyesus and Ato Animaw Azage to form the first parish council of our church. |
Soon, along with other faithful followers of Christ, the early members of Holy Trinity started holding weekly service, then by listening to the Holy Liturgy by tape. The original services were held at the Senior Center of Holy Trinity Greek Orthodox Church in Charlotte, through the kindness and encouragement of their members, and especially the-then Dean Father Nick Milas.
Through the will of God, we were soon blessed with our own first priest, Aba Woldetsadik Maregn and started providing Holy Liturgy service to the growing parishioners. Our church grew quickly and the need to have our own church home grew accordingly. Through the grace of Almighty God and the commitment and sacrifice of our members, within six short years, we were able to acquire land on Idlewild Road in Charlotte. With the kind assistance of our fellow Christians at Independence Hill Baptist Church, we were able to build our first (and current) church home on the site in July 2005.
Holy Trinity is now a thriving community of the followers of the Ethiopian Orthodox Tewahedo faith, among the oldest of Christian faith traditions in the world. We are working hard to uphold the tenets of the EOTC and offer a wide variety of services to strengthen the faith of our parishioners and to spread God’s kingdom on earth. We pray that this website helps to accomplish this objective.
May the blessings of the Holy Trinity be upon all of us, and may the Trinity continue to bless our church. May all glory be unto The Father, Son and Holy Spirit. Amen.
የቤተክርስቲያናችን አጭር ታሪክ
የታሪክን አደራ የተረዱና ለእምታችንና ለሃይማኖታችን በጽናት የቆሙ ወገኖች በሻርለት ከተማ ፀሎት የምናደርስበት አንድ ቤተክርስቲያን
ለማቋቋም በእግዚአብሔር ተገፋፍተው አንድ ዓመት ከፈጀ ከብዙ ድካም እና ቅድመ ዝግጅት በኋላ ሃሳቡ በAugust 10, 1999 ከኖርዝ ካሮላይና ጠቅላይ ግዛት፤ በመቀጠልም በ August 31, 1999 ከፌዴራሉ መንግስት በተገኙት ፈቃዶች አማካይነት እውን ሆኖ መካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ (“መካነ ብርሃን”) ልትመሠረት ቻለች።
ወደ ዝርዝሩ ስንገባ ደግሞ፤ የመጀመሪያዎቹ መሥራቾች ሦስት የከተማችን አባቶች አቶ ተድላ ፋንታዬ፣ አቶ እስጢፋኖስ አሰፋ እና አቶ ዮሴፍ አብርሃ ነበሩ። ከእነኚህ መሥራቾች ጋር አብረው በመሥራት የመጀመሪያ የመካነ ብርሃን የሰበካ ጉባዔ አባላት ሆነው ያገለገሉም ወ/ሮ ፋንታዬ ገመዳ እና ወ/ሮ አበበች አሰፋ፤ በመጨመርም ዶ/ር ተክሌ አያኖ፣ አቶ በላይ ገብረየሱስ እና አቶ አንማው ተናገር ነበሩ።
መካነ ብርሃን ስትጠነሰስ 600 East Blvd. ላይ በሚኘው የግሪኮች ካቴድራል አስተዳዳሪ ካህን በነበሩት በ Father Nick Milas መልካም ፈቃድ እና አበረታቺነት እንደቁጥራችን ማነስና መብዛት ከትንሽ እስከ መለስተኛ ክፍሎች እየፈቀዱልን በቴፕ ክር በቋንቋችን ቅዳሴና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንከታተል ነበር። መዘምራንም ዘወትር ቅዳሜ በወ/ሮ ሐረገወይን ኃይሌ ቤት እየተገኙ እርስ በእርሳቸው ይማማሩ ነበር።
በተጨማሪ ሳይጠቀሱ የማይታለፉት ባለውለታችን በወቅቱ አትላንታ ከተማ ይኖሩ የነበሩት ሊቀ ትጉሃን (ዛሬ ቀሲስ) የወንድወሰን ኩሩ ናቸው። እኚህ ካህን በራሳቸው ፈቃድ አልፎ፤ አልፎ እሁድ፤ እሁድ ከአራት ሰዓት በላይ ነድተው እየመጡ ትምህርትና የማበረታቻ ቃል ይሰጡን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የደብራችንን በመጀመሪያ አስተዳዳሪ ካህን አባታችንን አባ ወልደጻዲቅ ማረኝን አነጋግረው ያገናኙን እና ታቦተ ሕጉንም ከኢትዮጵያ ድረስ ያስመጡልን ታላቅ ባለውለታችን ናቸው።
ከኢትዮጵያ የተላከው ጽላት Washington, D.C. አርፎ በሊቀ ሊቃውንት አባ ወርቅነህ ኃይሌና በአባ መዓዛ በየነ አማካይነት ወደ ሻርለት ከመጣ በኋላ፤ በ July 1999 የሥላሴ ዓመታዊ በዓል በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ በደመቀ ሁኔታ ተከበረ። በዚህ ዕለት ብዙዎች ምዕመናን ቤተክርስቲያን በመከፈቱና ታቦተ ሕጉም በመምጣቱ የደስታ እንባ ሲተናነቃቸው ተስተውለዋል።
![]() |
![]() |
![]() |
![]() |
የመጀመሪያው የሥላሴ በዓል አከባበር
![]() |
እነዚህ አባቶች በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ በተደጋጋሚ ጊዜ ተመላልሰው አስተምረውናል፣አበረታተውናልም። ምንም እንኳን ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት አደራ መሆኑ ቢታወቅም እንኳ፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ከስድስት ሰዓት በላይ በመጓዝ እየተመላለሱ እራሳችንን እንድንችል አስችለውናል። በዚህም አጋጣሚ ላደረጉልን ትብብር ሁሉ ከልብ እናመሰግናቸዋለን፤ እግዚአብሔር አምላክ ውለታቸውን ይቁጠርልንም እንላለን። |
ከተመሠረተች ጀምሮ ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ ቤተክርስቲያናችን ያስመዘገበችው ዕድገት በማናቸውም መስፈርት ቢለካ የሚያኮራና የሚያስደስት መሆኑን ሌላ ዋቢ መጥቀስ አያስፈልግም፤ የሥራው ውጤትና ምዕመናኑ ማስረጃዎች ናቸውና። ከግሪክ ቤተክርስቲያን ጥገኝነት ሳይታክቱ በየሳምቱ ቅዳሜ መንበሩን እየገጠሙ፣ ታቦቱን እያጓጓዙ፤ ወንበር እየደረደሩ፣ አገልግሎት እንዲካሄድ ለደከሙ፤ እሁድ አገልግሎት ሲጠናቀቅም ያንን ሁሉ አንስተው፣ ሙሉ ጽዳት አጠናቀው ቦታውን እንደተረከብነው ለመመልስ ላስቻሉን አባቶች፣ ወንድሞች እና እህቶችም ከፍ ያለ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ከዚህ ደረጃ ተነስተን እንሆ ዛሬ የራሳችን የተንጣለለ ቦታ ገዝተን፤ የሥላሴን ቤት ገንብተን በነጻነት እና በባለቤትነት ከእዳ ነጻ ሆነን ለማምለክ ላስቻሉን ለአብርሃሙ ሥላሴ ክብር እና ምስጋና ለዘልዓለም ይሁን እንላለን።
የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ ተልዕኮ መንፈሳዊ እንደመሆኑ ከተጀመረ ጀምሮ በተለያየ ወቅት የመንፈሳዊ አግልግሎት ሳይቋረጥ ከፍተኛ መስዋ’ዕትነትን ከፍለው ለመሩን እና ላገለገሉን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ካህናትና አባቶች በተለይም ቆሞስ አባ ወልደጻዲቅ ማረኝ፣ ቆሞስ አባ ቤዛ ዓለሙ፣ አባ ሃብተማርያም ተፋለጥ፣ አባ ገ/ማርያም አሰፋ፣ ዲያቆን በጋሻው ወ/ሰንበት፣ ሊቀመዘምራን ፍስሐ ዘልዓለም፣ መሪጌታ ሰናይ አልማው፣ ቀሲስ በለጠ ሽመልስን፣ እና መሪጌታ ጥዑመልሳን ሰፊውን እና በርካታ ዲያቆናትን እና የሰንበት ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎችን እና መዘምራንን እጅግ ሳናመስግን አንዘጋም። በተመሳሳይ መልክ ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት አባቶችና ካህናት በተጨማሪ የአትላንታ ገብርዔል አስተዳዳሪ ጽባቴ የማነብርሃን አስራት ገብረማርያም፣ እንዲሁም የራሌ እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ አስተዳዳሪ ቀሲስ ክፍሉ ጉልትነህን ላበረከቱት አግልግሎትና ከፍተኛ አስተዋጽዖ ቤተክርስቲያናችን ዘወትር በአክብሮት ታስታውሳቸዋለች።
ማናቸውም የመንፈሳዊ ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንቅፋቶች እንደሚገጥሙት የሚታወቅ ነው። በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያናችን በተለያዩ የፈተና ወቅቶች ወስጥ ማለፏ የሚታወስ ሲሆን በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ያለው ፍቅር እና መንፈሳዊ ጥንካሬ በችግራችን ጊዜ እንደፋና እያበራ በእምነታችን ጸንተን ፈታናዎችን ለመቋቋም አስችሎናል። “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጧልና ይህም ጸጋ ኃጢአተኝነትን እና ዓለማዊ ምኞትን ክደን የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን አምላካችንን እና የመድኅኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን እራሳችንን በመግዛት እና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ 2፤ 11-14)
በመጨረሻም እላይ መክፈቻው ላይ ከተጠቀሱት መሥራች ወገኖች በተጨማሪ እስከ ሃሬ ድረስ ጊዜአቸውን ለሥላሴ እንደ መልካም መስዋዕት በማቅረብ ላገለገሉ፣ በእውቀታቸውና በገንዘባቸው የቤተክርስቲያናችንን ህልውና፣ አንድነት እና እድገት ላስከበሩ፣ አባላትን በማስተባበር ሥራዎች እንዲሠሩ እና በጋራ ችግሮችን ለመወጣት ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ የቤ/ክ የሰበካ ጉባዔ አባላትም የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን። የእነኚህ አባላት የሥም ዝርዝር እዚሁ ድረ-ገጹ ላይ ተዘርዝሮ ይገኛል።
ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ክብር እና ምስጋና ክብር ዛሬም ለዘልዓለምም ይሁን። እሱ ቸሩ አምላክ ድብራችንን እና አንድነታችንን ይጠብቅ፣ በሥራችንም ሁሉ እሱን እንድናስደስተውና እንድናኮራው ያብቃን።
“ትንሽ መወድስ”
መንፈስ የሚያድስ
(ይህ ስነጽሑፍ የቤተክርስቲያናችን መሥራቾች ከነበሩት እና በቅንነት እስከሕይወታቸው መጨረሻ ባገለገሉን በአቶ ተድላ ፋንታዬ የመካነ ብርሃንን 10ኛ ዓመት ለማክበር በተዘጋጀው መጽሔት ካቀረቡት የተወሰደ ነው። የአባታችንን ነፍስ በሰላም ያሳርፍልን።)
ለህጻናትና ለታዳጊ ወጣቶች አያታችሁ፤
ለጎልማሶች አባታችሁ፥
ለትልልቆች ወንድማችሁ
የሆንኩ ወገናችሁ
ቆሜአለሁ ከፊታችሁ
ለማለት እንኳን ደስ አለን፣ እንኳን ደስ አላችሁ።
የእግዚአብሔርን ሥራ ለማወደስ፤
በመቅደሱ ሆነን ስንል ቅዱስ፤ ቅዱስ፤ ቅዱስ፤
ሊሰማን ይገባል በእውነት የደስ ደስ።
መጀመሪያ ስናቅድ ጸሎት ቤታችንን ለማሠራት፤
እግዚአብሔርም ልመናችንን ሰማን በእውነት፤
ስናስታውስ የሱን ተዓምር፣
ሌሎች ክርስቲያኖችን በማስተባበር፤
ቤቱን ሠርቷል ውሎ ሳያድር።
በተጨማሪም ማን ይገኛል እንደኛ?
በምድረ እሜሪካ የሆነ እድለኛ፤
ፓንተርስን የሰጠን ለገቢ ማስገኛ።
እኛም በእግዚአብሔር ቸርነት ያገኘነውን እድል፤
በምንም ዓይነት ሳናጓድል፤
በሚያስመሰግን ሁኔታ አጠናቀነዋል በድል።
ያኔ፣ ያኔ የፓንተርስን ሥራ ስንጀምር፤
በአቶ ታዲዎስ ክፍሌ አማካይነት ነበር፤
እንዲያም ሲል በእነ አቶ ናፆድ አመራር ሥራው ተጠናክሮ፤
በእነ ዶ/ር ሰሎሞን እመርታውን አሳምሮ፤
እንደገና ወደ እነ አቶ ናዖድ ተዛውሮ፤
የአብርሃሙ ሥላሴ ሢሳይ ተጨምሮ፤
ከምንጊዜውም የበለጠ ህብረታችን ተጠናክሮ፤
እነሆ ገቢያችን ከፍ አለ ዘንድሮ
ለዚህም ማመስገን ይገባናል በሽብሸባ በከበሮ።
አሁንም እግዚአብሔር ይመስገን እንላለን፤
በረከቱን አሟልቶ ስላደለን።
ወገኖች፤ ገና አለብን ብዙ አደራ፤
ትልቁን የፀሎት ቤት ልናሠራ፤
በእግዚአብሔር ሆኖ ጽኑ እምነታችን፤
ሥላሴን አስቀድመን ከፊታችን፤
ቤዛን ይዘን ከጎናችን፤
ፍስሐ ወሰላም ከሆነ ደጃችን፤
የበለጠ ደጀን ተሰልፎ ከኋላችን፤
አንጠራጠርም ይሳካል ግባችን፤
አይተነዋልና ከተሞክሯችን።
እንዲሁም በመልካም አመራራችሁ የተመሰገናችጮ፤
የአሥተዳደር ጉባዔው አባላት የሆናችሁ፤
የቁጥጥር አባላትን ጨምራችሁ፤
ሁላችሁም በአንድነት ሆናችሁ፤
ባስገኛችሁት ውጤት ኮራንባችሁ።
ምግብ በማቅረብ የተባበራችሁ፤
ሕፃናትን የጠበቃችሁ፤
የፓንተርስን ሥራ እንደራሳችሁ አይታችሁ፤
በሁሉም የሥራ ዘርፍ የተሳተፋችሁ፤
ልባችሁ እያሰበ በአቅም ማነስ ወይም በሌላ ያልተሳተፋችሁ፤
በፀሎታችሁ እያሰባችሁ፤
አልተለየንም ድጋፋችሁ።
ስለዚህም ሥላሴዎች ይባርኳችሁ፤
በረከቱንም ይስጧችሁ።
ትናንት ህፃናት የነበራችሁ፤
ዛሬ አድጋችሁ የምናያችሁ፤
ትውፊቱን ተረካቢ ሆናችሁ፤
በመካከላችን በመገኘታችሁ፤
እያልን እንኳን ለዚህ አበቃችሁ፤
ተረከቡን ሁሉንም ይኸውላችሁ።
ሌሎችንም ታዳጊ ወጣቶችና ህፃናት፤
እግዚአብሔር ጠብቆ በጤንነት፤
እንዲያሳድግልን እየለመንን፤
እናንተም በተራችሁ ታሪክ ተረካቢዎች እንደምትሆኑ እናምናለን።
አያይዤም፤ እስቲ ላመስግን ወጣቶችን፤
የነገ ባለአደራዎችን፤
እየጠራሁ ስሞችን።
ልዋምና ሊዲያ አይዳና ሄለን፤
እንሴኔና ምዕራፍ ሃናን ጨምረን፤
ሩትና አህላም እንዲሁም አመል፤
ኖላዊና ብንያም ሚኪና ልዑል፤
ያሬድና ናሆም ወንድማማቾቹ፤
ማርቆስና ዮሴፍ ጓደኛማቾቹ፤
መንቲ ተሰማና ናቲ መኮንን፡
አርያም ሶፊያ ዮዲት ሰሎሞን፣
የሚታዘዙን እነ ሄኖክ፣
እነ አዲስና እነ ብሩክ፤
በኃይሉና ሱራፌል ታታሪዎቹ፣
ውጤት አስገኙልን ሁሉም ሳይሰለቹ።
አዎ አምላክን ይዘን ከጎናችን፣
አምሮልናል ውጤታችን።
እናም እንኮራባቸዋለን፣
ፈጥነው ስለደረሱልን።
ስለዚህ ለእነርሱ የምንከፍላቸው ቢኖር፤
መጸልይ ነው ወደ እግዚአብሔር፤
እንዲያበቃቸው ለቁም ነገር።
የሥላሴ ወዳጆች የሆናችሁ በሙሉ፤
በእስካሁኑ ያልተሳተፋችሁ ሁሉ፤
ወደፊትም ስለሚኖር እድሉ፤
የበረከቱ ተቋዳሾች እንድትሆኑ፤
ተመዝገቡ ዛሬውኑ፡፡
ቀደም ሲል ከእኛ ጋር ሆናችሁ፤
ሥላሴን በሁሉም መስክ ያገለገላችሁ፤
ዛሬ በመካከላችን የሌላችሁ፤
ለመልካም ተሳትፎአችሁ፤
የሥላሴዎች በረክት አይለያችሁ፤
ምስጋናችንም ይድረሳችሁ።
እንዲሁም መልካሙን ሁሉ በመመኘት ለሁላችን፤
ሰላምና ፍቅር እንዲኖር በመካከላችን፤
መትጋት አለብን እያንዳንዳችን።
ከአያት ከአባቶቻችን የወረስነው፤
ከመንፈሳዊ አባቶችም የተማርነው፤
መቻቻልና መከባበርን ጨምረን
ይቅር መባባልና ቂም አለመያዝን ነው፤
እኛም ለልጆቻችን የምንመኘው፤
ከላይ የጠቀስናቸውን መልካም ነገሮች እንዲወርቡ ነው=
በመሆኑም ቤተክርስቲያን የዚህ ሁሉ መሠረት መሆኗን እያስረዳናቸው፤
ቃሉን እያስተማርናቸው፤
ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን እንጠብቃቸው።
ግና ቸል ብለን ከእጃችን ቢያመልጡን፤
ኋላ አንችለውም ወቀሳውን።
ስለዚህም በጣም እንጠንቀቅ፤
ዓይናችን እያየ በአውሬ እንዳንነጠቅ።
በመጨረሻም በዚህች መወድስ ያልተጠራችሁ ፤
እያንዳንዳችሁን ደስ ይበላችሁ፤
በሥላሴዎች መዝገብ ተጽፏል ስማችሁ፤
የተቀደሰ ነውና ሥራችሁ።
እንግዲህ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነውና ብሂሉ፤
ለኔም ምስጋና ይገባኛል እንደሌሎች ሁሉ፤
እናም አጨብጭቡልኝ በሙሉ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን። አመሰግናለሁ። በተድላ ፋንታዬ 02/15/09 |
![]() |